ስለ ራስዎ፣ ቤተሰብዎ ወይም ወዳጅዎ የልብ ቀዶ ሕክምና ተጨንቀዋል?

እንግዲያውስ ይህንን መረጃ ይመልከቱ

(በዶ/ር አዘነ ደሴ መንግስቱ፤ በልብ ማዕከል የህፃናት የልብ ሐኪም)

ሀ. የቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው የልብ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው?

 • በተፈጥሮ በልብ ውስጥና ከልብ በሚነሱ ትልልቅ የደም ቱቦዎች ላይ የሚፈጠር ክፍተት ወይም ጥበት፡፡
 • በአብዛኛው በድህነት ላይ በሚገኙና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ከሚከሰቱ የልብ በሽታዎች ውስጥ ሌላው የቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው የልብ ደዌ የሪውማቲክ የልብ ህመም ሲሆን በዋናነት በሽታው የሚያስከትለው ችግርም የልብ በሮችን በመጉዳት ነው፡፡

ለ. ከልብ ቀዶ ህክምና በፊት በሕሙማን የሚከናወኑ ቅድመ ዝግጅቶች ምን ምን ናቸው?

 • የሰመመን መድኃኒቶችን ጨምሮ ከዚህ በፊት የተከሰተ የመድኃኒት አለርጂ ካለ ለሐኪሞች ማሳወቅ&
 • የተለየ የሐኪም ትዕዛዝ ካልኖረ በስተቀር በፊት ይወሰዱ የነበሩ መድሃኒቶችን አለማቋረጥ ይመከራል፡፡ ይሁንና እንደ ደም ማቅጠኛና ሌሎች በቀዶ ሕክምናው ሂደት ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ መድሃኒቶች የልብ ሐኪሞች በሚያዙት መሠረት ማስተካከያዎች ሊደረጉ ይችላሉ፡፡
 • የልብ በሮችን ቀዶ ህክምና ከመካሄዱ አስቀድሞ ባለፉት ስድስት ወራት የጥርስ ምርመራ ያላደረጉ ህሙማን ከቀዶ ህክምና በፊት የጥርስ ሐኪም ማማከር (Dental Clearance) እንዲያመጡ ይመከራል፡፡
 • ለልብ ቀዶ ህክምና ሆስፒታል ከመተኛት በፊት የተለያዩ የላቦራቶሪ ምርመራዎች እንደሚሠሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
 • ቀዶ ህክምናው በሚካሄድበት ቀን ጠዋት ላይ የልብ ህሙማን የፀረ-ባክቴሪያነት ባለው ሳሙና ገላቸውን ይታጠባሉ፡፡ በተጨማሪም ለቀዶ ህክምናው ቅድመ ዝግጅት በነርሶች የሚሠሩ ሌሎች ሥራዎች ይኖራሉ፡፡
 • ለቀዶ ጥገና የህክምና አገልግሎት የልብ ህሙማን ከመተኛታቸው በፊት በቅድመ ቀዶ ህክምና ስምምነት መግለጫ ፎርም  መሠረት መፈረም አለባቸው፡፡            በዚህም ወቅት በልብ ቀዶ ህክምና ሐኪም ስለሚሠራው ቀዶ ህክምናና ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮች የሚብራራ በመሆኑ ህሙማን (የህሙማን ወላጆች/አሳዳጊዎች) ከመፈረማቸው በፊት በአግባቡ መረዳት ተገቢ ነው፡፡
 • ታዳጊ የልብ ህሙማን ህፃናት ወደ ሆስፒታል እንዲተኙ ሲደረግ የተለያዩ ጥያቄዎች መጠየቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ ታዲያ ወላጆች ጥያቄያቸውን መሸፋፈን ሳይሆን እንደ ዕድሜያቸውና እንደብስለታቸው ሁኔታ የልባቸውን ችግር በሐኪሞች ለማስተካከል ሆስፒታል እንደተኙ ማስረዳት አለባቸው፡፡ ለልጆቻቸው በምን መልኩ ማስረዳት እንዳለባቸው የተቸገሩ ወላጆች የህፃናት የልብ ሐኪሞችን ማማከር ይችላሉ፡፡
 • የቀዶ ጥገናው ከሚካሄድበት ቀን ዋዜማ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ሐኪም በሚያዘው መሠረት ደረቅ ምግብ ለስድስት ሰዓት& ወተት ወይም ጁስ ለአራት ሰአት& ውሃ ወይም ሻይ ለሁለት ሰዓት መውሰድ አይኖርባቸውም፡፡ ይሁንና መወሰድ የሚገባው መድኃኒት ካለ በጠብታ ውሃ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሐ. በልብ ቀዶ ህክምና ወቅት (በቀዶ ህክምና ክፍል) የሚሠሩ ሥራዎች ምንድን  

   ናቸው?

 • የቀዶ ህክምናው ተግባራዊ የሚሆነው ለዚህ አገልግሎቶች በተዘጋጀ የቀዶ ህክምና ክፍል ነው፡፡
 • ቀዶ ጥገናው ሙሉ በሙሉ የሚካሄደው የሰመመን መድኃኒት ከተሰጠ በኋላ በመሆኑ ለሕሙማን የሚሠማ የህመም ስሜት አይኖርም፡፡
 • በአብዛኛው የልብ ቀዶ ህክምና የሚካሄደው ፊት ለፊት ደረትን በመክፈት ሲሆን ቀዶ ጥገናው በሚካሄድበት ወቅት ልብ ሥራዋን በጊዚያዊነት ታቆማለች፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ታካሚው የልብና የሳንባን ተፈጥሮአዊ ስራ በሚተካ ማሽን ላይ ይቆያል፡፡
 • የሚሠራው የቀዶ ህክምና ዓይነት እንደ ልብ በሽታው ሁኔታ ይለያያል፡፡
 • ቀዶ ጥገናው በሚካሄድበት ወቅት የታካሚውን ደህንነት መከታተል የሚያስችሉ የተለያዩ መሣሪያዎች በቀዶ ጥገናው ክፍሉ ይገኛሉ፡፡
 • በሰው ሰራሽ የልብና የሳንባ ማሽን ደጋፊነት የሚከናወን የልብ ቀዶ ጥገና በአማካይ ከ 3-6 ሰዓታት የሚወሰድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ልጆቻቸውን ወደ ቀዶ ጥገና ክፍሉ የላኩ ወላጆች ምናልባትም በህይወት ዘመናቸው በጣም ረዥሙና በውስጣቸው ውጥረት የሚነግስበት ሰዓታትን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ በዚህ ወቅት ወላጆች ከሆስፒታል ወጣ ብለው ተንቀሳቅሰው እንዲመለሱ ይመከራል፡፡

መ. የልብ ቀዶ ጥገና ከተጠናቀቀ በኋላ የሚደረጉ ህክምናዎችስ ምን ይመስላሉ?

 • የልብ ቀዶ ህክምናው ከተጠናቀቀ በኋላ ታካሚው ከቀዶ ጥገና ክፍል ወደ በጽኑ የታመሙ ታካሚዎች መከታተያ ክፍል (Intensive Care Unit) ይዛወራል፡፡
 • እንደ ልብ ህመሙ ደረጃ የሚሠራው ቀዶ ጥገና የሚለያይና ለሁሉም የማያስፈልግ ቢሆንም አንዳንድ ታካሚዎች ለ24 ሰዓትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ በሰው ሰራሽ የመተንፈሻ ማሽን (Ventillator) ላይ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
 • ከልብ ቀዶ ጥገና በኋላ ታካሚዎች ለመከታተልና መድኃኒት ለመስጠት የሚያገለግሉ የተለያዩ ቱቦዎች ይኖራሉ፡፡ እነሱም በሳንባ ዙሪያ ፈሳሽ እንዳይጠራቀም የሚረዳ ቲዩብ@ የኩላሊትን ትክክለኛ አሠራር ለመቆጣጠር የሚረዳ ከፊኛ ጋር የሚያያዝ ቲዩብና መድኃኒት ለመስጠትና ለመከታተል የሚያገለግሉ ከደም ሥር ጋር የሚያያዙ ቲዩቦች ናቸው፡፡
 • ከቀዶ ጥገና በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ዋና ችግሮች መድማት@ የልብ ምት ሥርዓት መዛባት@ ኢንፊክሽንና የኪላሊት ተፈጥሮአዊ አሠራር መዛባት ናቸው፡፡
 • በልብ በሮችን ቀዶ ህክምና ሰው ሠራሽ የብረት በር (Mechanical Valve) የተተካላቸው ታካሚዎች ቀዶ ጥገና ከመደረጋቸው በፊት ሰምተውት የማያውቁት የልብ ምት ድምፅ ስለሚሠሙ ይህን በመረዳት መደናገጥ የለባቸውም፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ህሙማን ዕድሜ ልክ የደም ማቅጠኛ (Blood thinners) መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
 • በደረት ላይ የሚገኘው ቀዶ ጥገና የተደረገበት ቁስል ቢያንስ ለ 48 ሰዓታት ተሸፍኖ ይቆያል፡፡
 • ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ህሙማን በራሳቸው መተንፈስ ሲችሉና በመከታተያ መሣሪያዎች ሁሉም ነገሮች ጥሩ ሆነው ሲገኙ የተለያዩ ቱቦዎች ከወጡ በኋላ በፅኑ ከታመሙ ታካሚዎች መከታተያ ክፍል (ICU) ወጥተው ወደ ዋርድ ይዛወራሉ፡፡ ከዚያም ሁኔታዎች ከተስተካከሉ በኋላ ህሙማን የተለያዩ መድኃኒቶች ከታዘዘላቸውና አጭር የቀጠሮ ጊዜ ተሰጥቷቸው ወደ ቤት ይሄዳሉ፡፡

4 thoughts on “ስለ ራስዎ፣ ቤተሰብዎ ወይም ወዳጅዎ የልብ ቀዶ ሕክምና ተጨንቀዋል?”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *