ደም እንዳይረጋ የሚረዳ (የደም ማቅጠኛ) መድኃኒት (Warfarin) ምንነት እና አጠቃቀም

በዶ/ር አዘነ ደሴ መንግስቱ፣ የህፃናት የልብ ሀኪም

. ለመሆኑ የደም ማቅጠኛ መድኃኒት ምንድን ነው?

የደም ማቅጠኛ መድኃኒት በአብዛኛው ሰው ሰራሽና ብረት-ነክ የሆነ የልብ ቫልቭ በኦፕራሲዎን ለገባላቸው ህሙማን የሚሰጥ መድኃኒት ነው፡፡ በሀገራችንና በሌላውም ዓለም ለዚህ አገልግሎት የሚውለው መድኃኒት ዋርፋሪን (warfarin) ይባላል፡፡ ከዋርፋሪን በተጨማሪ ወይም ለብቻው  አስፕሪንም እንደ ደም ማቅጠኛ መድኃኒነትነት ያገለግላል፡፡ በነገራችን ላይ የመድኃኒቶቹ አሠራር የሰው ደም ማቅጠን ሳይሆን ደም እንዳይረጋ ማድረግ ነው፡፡

. ደም እንዳይረጋ የሚወሰድ መድኃኒት አጠቃቀምን እንዴት መከታተል ይቻላል?

የዋርፋርን ዋና ጥቅሙ የደም መርጋትን ለመቀነስ ሲሆን መድኃኒቱ በትክክል እየሠራ መሆኑን ማወቅና መከታተል የሚቻለው እንደ አስፈላጊነቱ በየጊዜው በሚሠራ የደም ናሙና ምርመራ ነው፡፡ አለም አቀፋዊ ይዘት ያለው የደም መርጋትና አለመርጋትን መለኪያ አሀድም አይ ኤን አር (INR) የሚባል ሲሆን ትክክለኛ የሚባለው ቁጥርም እንደ ሰው ሰራሽ የልብ ቫልቩ ዓይነትና በልብ ውስጥ የተቀመጠበት ቦታ  ይለያያል፡፡ በመሆኑም ለሐኪም ሳያውቁ የመድኃኒቱን መጠን (Dose) መጨመር ወይም ቀንሶ መውሰድ አይመከርም፡፡

ሐ. የደም ማቅጠኛ መድኃኒት ዋና የጎንዮሽ ችግር (side effect) ምንድን ነው?

የዚህ መድኃኒት ዋና የጎንዮሽ ችግሮች መድማት ሲሆን በማንኛውም የሠውነት አካል ክፍሎች ሊከሰት ይችላል፡፡ በተለይም በጭንቅላት ውስጥ መድማት ከተከሰተ በህይወት ላይ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል የዋርፋሪን መድኃት የሚወስዱ ህሙማን ልዩ የባለሙያ ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም ህሙማኑ በሌላ የጤና ችግር ምክንያት ተጨማሪ መድኃኒት ከመታዘዙ በፊት ዋርፋሪን አንደሚወስዱ ለባለሙያ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ይህም የሚያሰፈልግበት ምክንያት አንዳድ መድኃኒቶች የዋርፋሪንን የደም ማቅጠን አሠራር ስለሚያዛቡ ነው፡፡

መ. የደም ማቅጠኛ መድኃኒት የሚወስዱ ህሙማን የአመጋገብ ሁኔታ ምን መምሰል ይኖርበታል?

ዋርፋሪን የሚወስዱ ህሙማን ወጥ የሆነና በእጅጉ የማይቀያየር የአመጋገብ ሥርዓት አንዲኖራቸው ይመከራሉ፡፡ በይዘታቸው ከፍተኛ ቫይታሚን ኬ ያላቸው እንደ ስላጣና ቆስጣ ያሉ ምግቦች የዋርፋሪንን ደም እንዳይረጋ የማድረግ ሥራ የሚያዛቡ በመሆናቸው ባይወሰዱ መልካም ነው፡፡በተጨማሪም የደም ማቅጠኛ መመድኃኒት የታዘዘላቸው ህሙማን አልኮል መጠጣት የለባቸውም፡፡

  ምስል 2፡  በውስጣቸው ከፍተኛ ቫይታሚን ኬ ያላቸውና የዋርፋሪንን ደም እንዳይረጋ የማድረግ ሥራ የሚያዛቡ አትክልትና ፍራፍ_ዎች 

ሠ. ነፍሰ ጡር የሆኑ የልብ ህሙማን እናቶች ዋርፋሪን መውሰድ ይችላሉን?

ዋርፋሪን  ከእናት ወደ ፅንስ መተላለፍ ሰለሚችልና በፅንሱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስከትል በመሆኑ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የእርግዝና ወቅት ባይወሰድ ይመከራል፡፡ በመሆኑም ዋርፋሪን የሚወስዱ የልብ ህሙማን እናቶች ልጅ ለመውለድ ከወሰኑ ከማርገዛቸው በፊት ባለሙያ ማማከር ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን ዋርፋሪን የምትወስድ እናት ለልጇ ጡት ማጥባት ትችላለች፡፡

ረ. ዋርፋሪን የሚወስዱ የልብ ህሙማን በአስቸኳይ የጤና ባለሙያ ማማከር ያለባቸው መቼ ነው?

የደም ማቅጠኛ መድኃኒት የሚወስዱ ህሙማን የሚከተሉትን ችግሮች ካስተዋሉ ወዲያውኑ ባለሙያ ማማከር አለባቸው፣

  • ያልተለመደና ከፍተኛ ራስ ምታት እንዲሁም የሰውነት አካል መስነፍ
  • የመድማት ችግሮች (ነስር፣ የሽንትና ዓይነ ምድር ቀለም መጥቆር፣ በትውከት ላይ ደም መታየት)
  • በተሸከርካሪ ወይም በሌላ ምክንያት የመድማት አደጋ መፈጠር
  • በወር አበባ ወቅት ያልተለመደ የጊዜ መዛባትና ብዙ ደም መፍሰስ ሲኖር
  • ኦፕራሲዎን የሚያስፈልገው የጤና ችግር ሲከሰት

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *